settings icon
share icon
ጥያቄ፤

ክርስትና ምንድ ነው? ክርስቲያኖች በምን ያምናሉ?

መልስ፤


1ኛ ቆሮንቶስ 15፡1-4 እንዲህ ይላል “ወንድሞች ሆይ፣ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን፣ በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፣ በከንቱ ካላመናችሁ በቀር፣ ብታስቡት፥ በምን ቃል እንደ ሰበክሁላችሁ አሳስባችኋለሁ። እኔ ደግሞ የተቀበልኩትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ። እንዲህ ብዬ፦ መፅሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለኃጢያታችን ሞተ፣ ተቀበረም፤ መፅሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሳ።”

በአጭሩ የክርስትና እምነት መሰረት ይህ ነው። ከሌሎች እምነቶች በተለየ መልኩ ከሐይማኖታዊ ልምምድ ይልቅ ክርስትና የሚያተኩረው በግንኙነት ላይ ነው። ይህን “አድርግና አታድርግ” የሚል መመሪያ ከመዘርዘር ይልቅ የክርስቲያን ግብ ከእግዚሐብሔር አባት ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዲኖር ያበረታታል። ያ ግንኙነት እውን ሊሆን የቻለው በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራና መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያኑ ሕይወት በሚኖረው አገልግሎት ነው።

መፅሐፍ ቅዱስ የእግዚሐብሔር መንፈስ ያለበትና ስህተት የሌለበት፣ ትምህርቱም የመጨረሻ ስልጣን ያለው መሆኑን ክርስቲያኖች ያምናሉ። (2ኛ ጢሞቲዎስ 3፡ 16፣ 2ኛ ጴጥሮስ 1፡ 20-21)። ክርስቲያኖች በሦስት አካላት በሚኖር በአንድ እግዚሐብሔር ያምናሉ። ይኸውም በአብ፣ በወልድ(በኢየሱስ ክርስቶስ) እና በመንፈስ ቅዱስ ነው።

የሰው ልጅ የተፈጠረው በተለይ ከእግዚሐብሔር ጋር ግንኙነት ለማድረግ እንደሆነ ክርስቲያኖች ያምናሉ። ነገር ግን ኃጢአት ሁሉንም ሰዎች ከእግዚሐብሔር አለያይቶአቸዋል። (ሮሜ 3፡ 23፣ 5፡ 12)። ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ሲመላለስ ፍፁም አምላክ፣ ፍፁም ሰው ሆኖ እንደኖረና በመስቀል ላይ እንደሞተ ክርስቲያኖች ያምናሉ።( ፊሊጲስዩስ 26፡ 6-11)። በመስቀል ላይ ከሞተ በኋላ ክርስቶስ ተቀብሮ እንደገና በመነሳት አሁን በአባቱ ቀኝ ሆኖ ለአማኞች ለዘላለም እንደሚማልድ ክርስቲያኖች ያምናሉ።(ዕብራውያን 7፡ 25)። የኢየሱስ በመስቀል ላይ መሞት ሁሉም ሰዎች በኃጢያት ምክንያት የነበረባቸውን ዕዳ ለመክፈል ብቁ እንደሆነ ክርስትና ያምናል። ይህ ነው እንግዲህ በእግዚሐብሔርና በሰው መካከል ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት እንዲታደስ ያደረገው ነገር።( ዕብራውያን 9፡ 11-14፣ 10፡ 10፣ ሮሜ 5፡8፣ 6፡ 23)።

አንድ ሰው ለመዳን ከፈለገ በመስቀሉ ላይ በተፈፀመው የክርስቶስ ሥራ እምነቱን ማኖር አለበት። ማንም ሰው ክርስቶስ በእርሱ ፋንታ እንደሞተና ለራሱ ኃጢያት ዋጋ እንደከፈለለት እንደገናም እንደተነሳ ካመነ፣ ያ ሰው ድነት አግኝቷል ማለት ነው። ማንም ሰው ድነትን ለማግኘት ምንም ማድረግ አይችልም። ማንም ግለሰብ በራሱ ወይም በራስዋ “መልካም በማድረግ” እግዚሐብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም። ምክንያቱም ሁላችንም ኃጢያተኞች ስለሆን። (ኢሳያስ 53፡ 6፣ 64፡ 6-7)። ሁለተኛም ከዚህ የበለጠ የሚሰራ ሥራ የለም። ምክንያቱም ክርስቶስ ሁሉን ሥራ አከናውኖታል! በመስቀል ላይ ሆኖ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል “ተፈፀመ” (ዮሐንስ 19፡ 30)።

ድነትን ለማግኘት ማንም ምንም ማድረግ እንደሌለበት ሁሉ እርሱ/እርሷ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሰራው ሥራ ከታመኑ በሌላው በኩል ደግሞ እርሱ/እርሷ ድነታቸውን ለማጣት ምንም ማድረግ የለባቸውም። ምክንያቱም ሥራው ተሰርቶ ያለቀው በክርስቶስ በመሆኑ! ድነት በምንም መንገድ በተቀባዩ ላይ የተመሰረተ አይደለም። ዮሐንስ 10፡ 27-29 እንዲህ ይላል “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፣ እኔም አውቃቸዋለሁ፣ ይከተሉኝማል፣ እኔም የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፣ ለዘላለምም አይጠፉም፣ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፣ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም።”

አንዳንዶች እንዲህ ሊያስቡ ይችላሉ። “ይህ ትልቅ ነገር ነው- አንዴ ድነትን ካገኘሁ ያሻኝን እያደረግሁ ድነቴን ላጣ አልችልም!” ድነት ግን ነፃ ሆኖ የፈለጉትን ማድረግ ማለት አይደለም። ድነት ማለት የድሮውን የኃጢያት ተፈጥሮ ከማገልገል ነፃ በመሆን ከእግዚሐብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት ለማራመድ ነፃ መውጣትን ነው የሚያሳየው። ከዚህ ቀደም ለኃጠያት ባርያዎች ነበርን፤ አሁን ግን እኛ የክርስቶስ ባርያዎች ነን። (ሮሜ 6፡ 15-22)። አማኞች በዚህ ዓለም ላይ ከኃጢያተኛው ተፈጥሮአቸው ጋር እስካሉ ድረስ፣ ከኃጢያት ጋር የማያቋርጥ ትግል እንደሚያደርጉ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ከኃጢያት ጋር በሚያደርጉት ትግል ክርስቲያኖች ድል ሊቀዳጁ የሚችሉበት መንገድ አለ። የእግዚሐብሔር ቃል (መፅሐፍ ቅዱስ) በማጥናትና በሕይወታቸው በመተግበር፣ ራሳቸውን በመንፈስ ቅዱስ ሥር በማዋል፣ የእግዚሐብሔርን ቃል በመታዘዝ፣ የዕለት ተዕለት ኑሮአቸው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንዲመራ መፍቀድ ይጠበቅባቸዋል። ስለዚህ በርካታ የእምነት ሥርዓቶች የተወሰኑ ነገሮችን እንዲያደርጉ ወይም እንዳያደርጉ ግዴታ ሲጥሉ፣ ክርስትና ግን የእኛን የኃጢያት ዋጋ ለመክፈል ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሞቶ እንደገና እንደተነሳ ማመን ብቻ ነው የሚጠይቀው። ያንተ የኃጢያት ዕዳ ተከፍሏል። ስለዚህ ከእግዚሐብሔር ጋር ሕብረት ማድረግ ትችላለህ። በኃጢያተኛው ተፈጥሮህ ላይ ድል በመቀዳጀት፣ ለእግዚሐብሔር በመታዘዝ፣ ከእርሱ ጋር በሕብረት ለመራመድ መንገድ ተከፍቶልሐል። ይህ ነው እንግዲህ እውነተኛው መፅሐፍ ቅዱሳዊ ክርስትና ማለት።

English



ወደ አማርኛ መነሻ ገጽ ለመመለስ

ክርስትና ምንድ ነው? ክርስቲያኖች በምን ያምናሉ?
© Copyright Got Questions Ministries