settings icon
share icon
ጥያቄ፤

የቤተ ክርስቲያን መነጠቅ ምንድነው?

መልስ፤


“መነጠቅ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ቢሆንም፣ የመነጠቅ ጽንሰ-ሐሳብ በቅዱስ ቃሉ በግልጽ ተስተምሯል። የቤተ ክርስቲያን መነጠቅ፣ እግዚአብሔር ሁሉንም አማኞች ከምድር ላይ የሚወስድበት ሁነት ነው፣ የጽድቅ ፍርዱን በምድር ላይ ከማፍሰሱ በፊት መንገዱን የሚያመቻችበት፣ በታላቁ መከራ ጊዜ። መነጠቅ በቅድሚያ የተገለጸው በ1 ተሰሎንቄ 4:13-18 እና 1 ቆሮንቶስ 15:50-54 ላይ ነው። እግዚአብሔር የሞቱትን አማኞች ሁሉ ያስነሣቸዋል፣ የከበረ አካልም ያለብሳቸዋል፣ ከምድርም ይወስዳቸዋል፣ በሕይወት ካሉት አማኞች ጋር፣ እነሱም ደግሞ በዛን ጊዜ የከበረ አካል የሚሰጣቸው። “ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን” (1 ተሰሎንቄ 4፡16-17)።

መነጠቅ በባሕርዩ ቅጽበታዊ ይሆናል፣ በዛን ሰዓትም የከበረውን አካል እንቀበላለን። “እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን” (1 ቆሮንቶስ 15፡51-52)። መነጠቅ ሁላችንም በተስፋ መጠበቅ የሚኖርብን የከበረ ሁነት ነው። በመጨረሻም ከኃጢአት ነጻ እንወጣለን። ከእግዚአብሔር መገኘት ጋር ለዘላለም እንሆናለን። እጅግ በርካታ ክርክሮች ከመነጠቅ ፍቺ እና ከስፋቱ አኳያ ተካሂደዋል። ይህ የእግዚአብሔር ሐሳብ አይደለም። ይልቁንም፣ መነጠቅን በተመለከተ፣ እግዚአብሔር “እርስ በርሳችን በዚህ ቃል እንድንጽናና” ይፈልጋል፣ (1 ተሰሎንቄ 4፡18)።

English



ወደ አማርኛ መነሻ ገጽ ለመመለስ

የቤተ ክርስቲያን መነጠቅ ምንድነው?
© Copyright Got Questions Ministries