ጥያቄ፤
ክርስቲያን ማን ነው?
መልስ፤
ዌብስተር መዝገበ ቃላት ክርስቲያን ማለት “በክርስቶስ የሚያምን ወይንም በክርስቶስ ትምህርት በተመሠረተ ሃይማኖት የሚያምን ሰው” ነው ሲል ያስቀምጠዋል። የክርስቲያን ምንነት ለመረዳት ይህ የዌብስተር ፍች መነሻ ሊሆነን ይችላል፤ ነገር ግን ልክ እንደሌሎቹ ዓለማዊ የሆኑ ፍችዎች ክርስቲያን መሆን የሚያመለክተውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ማስተላለፍ አይችልም።
ክርስቲያን የሚለው ቃል በሐዲስ ኪዳን ሦስት ጊዜ ተጠቅሶ እናገኝዋለን (የሐዋርያት ሥራ ፲፩፥፳፮፤ የሐዋርያት ሥራ ፳፮፥፳፰፤ ፩ኛ ጴጥሮስ ፬፥፲፮)። የኢየሱስ ተከታዮች ክርስቲያን የሚል ስም በመጀመሪያ በአንጾኪያ ተሰጣቸው (የሐዋሪያት ሥራ ፲፩፥፳፮)፤ ይህም ስም የተሰጣቸው ሥራቸውና ጸባያቸው እንደክርስቶስ ስለነበር ነው። በመጀመሪያ ይህ ስም ያልዳኑት የአነጾኪያ ሰዎች ክርስቲያን የሆኑትን ላይ ለማላገጥ ያወጡላቸው ስም ነበር። ቀትተኛ ተርጉሙም፣ “የክርስቶስ ማኀበር አባል” ወይንም “የክርስቶስ ተከታይ” ማለት ነው።
ቢሆንም ከጊዜ በኋላ “ክርስቲያን” የሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉሙ አጥቶ የክርስቶስ ተከታይ ለሆነው ሳይሆን ግብረ ገባዊ በሆነ መንገድ ለሚመላለስ ማንኛውንም ሃይማኖተኛ የሚሰጥ ስም ሆኖ እናገኘዋለን። ብዙ ሰዎች በ ኢየሱስ ክርስቶስ ባያምኑም አንኳን ወደ ቤተ ክርስቲያን በመመላለሳቸው ወይንም “ክርስቲያን” በሆነ አገር በመኖራቸው ብቻ ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው ይሰይማሉ። ቢሆንም ግን ወደ ቤተ ክርስቲያን መመላለስ፣ ካነተ በታች የሆኑትን መርዳትና ጥሩ ሰው ሆኖ መገኘት ብቻ በራሱ ክርስቲያን አያደርግህም። አንድ ሰባኪ እንዳለው፣ “ወደ ቤተ ክርስቲያን መመላለስ አንድን ሰው ክርስቲያን አያደርገውም፤ ልክ ወደ ጋራዥ መመላለስ አንድን ሰው መኪና እንደማያደርገው ሁሉ።” የቤተ ክርስቲያን አባል መሆን፣ ጉባኤ መከታተልና የቤተ ክርስቲያንን ሥራ መሥራት ብቻ ክርስቲያን አያደርግህም።
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን የምንሠራው በጎ ሥራ ብቻውን በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን አያስገኝልንም። ቲቶ ፫፥፭ እነዲህ ይለናል፤ “ስላደረግነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን፣ ከምሕረቱ የተነሣ አዳነን። ያዳነንም ዳግም ልደት በሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ ነው።” ስለዚህ፣ ክርስቲያን ማለት በእግዚአብሔር እንደገና የተወለደና (ዮሐንስ ፫፥፫፤ ዮሐንስ ፫፥፯፤ ፩ኛ ጴጥሮስ ፩፥ ፳፫) እምነቱንም በክርስቶስ ያደረገ ሰው ነው። ኤፌሶን ፪፥፰ እነደሚለን፣ “በእምነት፣ በጸጋ ድናችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከ እናንተ አይደለም።” እውነተኛው ክርስቲያን ለኀጢአቱ ንስሓ የገባና በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ያመነ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች እምነታቸው ሃይማኖትን፣ ግብረ ገባዊ ሕጎችንና “አድርግ አታድርግ” ዝርዝሮችን ላይ አይደለም።
እውነተኛ ክርስቲያን እምነቱ በክርስቶስ ያደረገ፣ ክርስቶስ መስቀል ላይ የሞተው ለኀጢአታችን ሲል እነደሆነና በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተነስቶ ሞት ላይ አቸናፊነቱን ያረጋገጠው በሱ ለሚያምኑ ዘለዓለማዊ ሕይወትን ለመስጠት መሆኑን ያመነ ማለት ነው። ዮሐንስ ፩፥፲፪ እንዲህ ይለናል፤ “ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑት ሁሉ ግን የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን መብት ተሰጣቸው።” እውነተኛው ክርስቲያን የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤ እንዲሁም የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባልና በክርሰቶስ አዲስ ሕይወት የተሰጠው ነው። የእውነተኛ ክርስቲያን መለያ ለሌሎች በሚያሳየው ፍቅርና ለእግዚአብሔር ቃል በሚያሳየው መታዘዝ ነው (፩ኛ ዮሐንስ ፪፥፬፤ ፩ኛ ዮሐንስ ፪፥፲)።
እዚህ ባነበብከው ምክንያት ለክርስቶስ ውሳኔ ላይ ደርሰሃል? እንዲያ ከሆነ፣ “ዛሬ ክርሰቶስን ተቀብያለሁ” የሚለውን ቁልፍ ተጫን
English
ክርስቲያን ማን ነው?