ጥያቄ፤
ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?
መልስ፤
ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው? “እግዚአብሔር አለ” እነደሚለው ጥያቄ ሳይሆን፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መኖር በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው የሚጠራጠሩት። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት በእስራኤል ምድር የተመላለሰ ሰው እንደሆነ በአብዛኛው ተቀባይነት አለው። ክርክሩ የሚጀመረው የኢየሱስ ክርስቶስን እውነተኛ ማንነትን በተመለከተ ነው። ሁሉም አበይት ሃይማኖቶች ኢየሱስ ክርስቶስ ነቢይ፣ ወይም ጥሩ መምህር፣ ወይም አምላካዊ ሰው እንደነበር ያስተምራሉ።
ሲ. ሰ. ለዊስ “ባዶ ክርስትና” በሚል መጽሐፉ የሚከተለውን እናገኛለን፤ “ብዙ ሰዎች ስለእርሱ (ኢየሱስ ክርስቶስ) የሚሉትን ሞኝ የሆነ አባባል ለማስቀረት እየጣርኩ ነው፤ ‘ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ታላቁ የግብረ ገብ መምህሬ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፤ ነገር ግን አምላክነቱን አልቀበለውም።’ ይህ ነው እንግዲህ ማለት የሌለብን። ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውንና የሠራውን ሁሉ በአንድ ተራና የግብረ ገብ መምህር በሆነ ሰው በቻ ሊከናወን አይችልም። እንዲህ አይነቱ ሰው ወይም እብድ መሆን አለበት፣ አልያም የገሃነም ሰይጣን መሆን አለበት። መምረጥ አለብህ። ይህ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ነበር፣ ነውም፣ ወይንም ደግሞ እብድ ወይም ከዛም የባሰ ነበር ማለት ነው። ሞኝ ነው ብለህ ልታልፈው፣ ልትተፋበትና ጋኔን ነው በለህ ልትገድለው ትችላለህ፤ ወይንም ደገሞ ጌታየና አምላኬ ብለህ እግሩ ሥር ልትደፋለት ትችላለህ። ነገር ግን ዝቅተኛ መንፈስ በሚያሳይ መልኩ ታላቅ ሰብአዊ መምህር እያላን ግን አንመጻደቅ። ይህ ከምርጫዎቹ ውስጥ የለም። የዚህ አይነት ምርጫ እንዲኖረንም ዕቅዱ አልነበረም።”
ስለዚህ፣ ክርስቶስ ማን ነኝ ብሎ አወጀ? መጽሐፍ ቅዱስስ ስለማንነቱ ምን ይለናል? በመጀመሪያ የኢየሱስን ቃል በዮሐንስ ፲፥፴ የተጻፈውን እንመልከት፤ “እኔና አብ አንድ ነን።” ላዩን ብቻ ሲታይ፣ የአምላክነት አዋጅ ላይመስለን ይችላል። ነገር ግን ለዚህ ቃሉ የአይሁድን መልስ ማየት ብቻ በቂ ነው፤ “የምንወግርህ፣ ተራ ሰው ሆነህ ሳለህ፣ ራስህን አምላክ በማድረግ፣ የስድብ ቃል ስለተናገርህ ነው እንጂ ከእነዚህ ስለየትኛውም አይደለም” (ዮሐንስ ፲፥፴፫)። አይሁድ የክርስቶስ ንግግር የአምላክነቱን አዋጅ መሆኑ ገባቸው። በሚቀጥሉት ጥቅሶች ኢየሱስ አይሁድን “አምላክ አይደለሁም” ብሎ ሲያርማቸው አይታይም። ይህም የሚያመለክተው ኢየሱስ በአውነት የአምላክ ልጅ እንደሆነ መናገሩን ነው፤ “እኔና አብ አንድ ነን” (ዮሐንስ ፲፥፴)። ዮሐንስ ፰፥፶፰ ደግሞ ሌላው ምሳሌ ነው፤ “ኢየሱስም፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፤ አብራሃም ከመወለዱ በፊት እኔ፣ እኔ ነኝ’ አላቸው።” ለዚህ መልሱም አይሁድ በድንጋይ ሊወግሩት ሞከሩ (ዮሐንስ ፰፥፶፱)። ኢየሱስ ስለማንነቱ “እኔ ነኝ” ብሎ መናገሩ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ይጠራበት የነበረውን ስም መጠቀሙን ያሳየናል (ዘፀአት ፫፥፲፬)። ታድያ እነርሱ እንደስድብ በቆጠሩት የአምላክነቱን አዋጅ ካልሆነ በቀር በሌላ በምን ምክንያት አይሁድ ኢየሱስን በድንጋይ ሊወግሩት ተነሳሱ?
ዮሐንስ ፩፥፩ እንደሚለው “… ቃልም እግዚአብሔር ነበር።” በማሰከተልም፣ ዮሐንስ ፩፥፲፬ “ቃልም ሥጋ ሆነ” ይላል። ይህ በግልጽ እንደሚያመለክተው ክርስቶስ ሥጋ የለበሰ አምላክ ነው። የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ቶማስ፣ “ጌታየ፤ አምላኬም!” በማለት የኢየሱስን አምላክነት ተናገረ (ዮሐንስ ፳፥፳፰)። ለዚህ ንግግሩም ኢየሱስ አልገሰጸውም። የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ጳውሎስ እንዲህ በማለት ኢየሱስን ይገልጸዋል፤ “…የታላቁን የአምላካችንንና የአዳኛችን የኢየሱስ ክርስቶስ…” (ቲቶ ፪፥፲፫)። የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ጴጥሮስም ተመሳሳዩን ይናገራል፤ “…በአምላካችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ…” (፪ኛ ጴጥሮስ ፩፥፩)። እግዚአብሔር አብም ስለ ኢየሱስ ሙሉ ማንነት እነዲህ ሲል ይመሰክራል፤ “…አምላክ ሆይ፤ ዙፋንህ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፤ ጽድቅም የመንግሥትህ በትር ይሆናል” (ዕብራውያን ፩፥፰)። የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ስለ ክርስቶስ አምላክነት እንዲህ ይላሉ፤ “ሕፃን ተወልዶልናልና፤ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል። ስሙም፣ ድንቅ መካር፣ ኀያል አምላክ፣ የዘለዓለም አባት፣ የስላም ልዑል ይባላል” (ኢሳይያስ ፱፥፮)።
ስለዚህ፣ ኢየሱስ እንደ አንድ ጥሩ መምህር ብቻ መቀበል ምርጫ ውስጥ የለም ሲል ሲ. ሰ. ለዊስ ይከራከራል። አምላክ ካለሆነ ዋሽቶአል ማለት ነውና ነብይም ሆነ ጥሩ መምህር ሊሆን አይችልም። አንዳድ ዘመናውያን “ሊቃውንት” የኢየሱስን ቃል እርሱ እንዳልተናገረው ለማስመሰል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ኢየሱስ የተጠቀሰው ሁሉ፣ “እውነተኛው የታሪክ ኢየሱስ” በቃሉ አልተናገረውም ይላሉ። እኛ ማን ነንና ኢየሱስ ስላለው ወይም ስላላለው ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የምንከራከረው? እንዴት ሲሆን ነው አንድ “ሊቅ” የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት የተደረገውን ከኢየሱስ ጋር አብረው ከነበሩት በላይ ሊያውቅ የሚችለው?
ስለ ኢየሱስ ማንነት ጥያቄ ለምንድነው እንደዚህ አንገብባቢ የሆነው? ኢየሱስ አምላክ ቢሆንም ባይሆንምስ ለምን ጉዳያችን እናደርገዋለን? ዋናው ምክንያት፣ ኢየሱስ አምላክ ካልሆነ፣ ሞቱ የዓለምን ኀጢአት ለማስተሰረይ አይችልም ማለት ነው (፩ኛ ዮሐንስ ፪፥፪)። አምላክ ብቻ ነው እንደዚህ ያለ መጨረሻ የሌለው ቅጣት መቀበል የሚችለው (ሮሜ ፭፥፰፤ ፪ኛ ቆሮንቶስ ፭፥፳፩)። ኢየሱስ አምላክ መሆን አለበት ዕዳችንን እንዲከፍልልን። ኢየሱስ ሰው መሆን ነበረበት መሞት እንዲችል። ድነት የሚገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው! የኢየሱስ አምላክነትም ነው የድነት መንገድ በኢየሱስ ብቻ እንዲሆን ያደረገው። ኢየሱስ አምላክ ስለሆነም ነው እንዲህ ብሎ ያወጀው፤ “መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካለሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” (ዮሐንስ ፲፬፥፮)።
English
ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?